ሥራ እየፈለጉ ነው? ስህተቶችን ያስወግዱ እና የስራ እድልዎን ያሳድጉ!

✨ ሥራ እየፈለጉ ነው? ስህተቶችን ያስወግዱ እና የስራ እድልዎን ያሳድጉ!
ብዙ ሰዎች ሥራ ለማግኘት ሲያመለክቱ ሳያውቁት ስህተቶችን ይሰራሉ። እነዚህ ስህተቶች ደግሞ ተቀጥረው የመሥራት ዕድላቸውን በእጅጉ ይቀንሳሉ። እርስዎም በተደጋጋሚ ሥራ አመልክተው ውጤት እያጡ ከሆነ፣ የሚከተሉትን ነጥቦች በጥንቃቄ በማንበብ ስህተቶችዎን ማረም እና ተፈላጊነቶን ማሳደግ ይችላሉ።
1. የሥራ ማስታወቂያውን በጥንቃቄ ማንበብ እና መረዳት
ይህ በጣም መሰረታዊ እና ወሳኝ እርምጃ ነው። ብዙ አመልካቾች የስራ ማስታወቂያውን ዝርዝር ጉዳዮች ሳያነቡ ወይም ላዩን ብቻ አይተው ማመልከት ይጀምራሉ። ይህ ደግሞ ለብዙ ስህተቶች መነሻ ይሆናል።
● መስፈርቶችን ሙሉ በሙሉ ያሟሉ: ማስታወቂያው የሚፈልገውን የትምህርት ደረጃ፣ የስራ ልምድ፣ ልዩ ችሎታዎች እና ሌሎች መስፈርቶችን በጥንቃቄ ያንብቡ። የድርጅቱ ፍላጎት ከእርስዎ ብቃት ጋር የማይሄድ ከሆነ፣ ጊዜዎን እና የድርጅቱን ጊዜ አያባክኑ።
● የሚጠየቁ ሰነዶችን በትክክል ያቅርቡ: ሲቪ (CV)፣ የሽፋን ደብዳቤ (Cover Letter)፣ የትምህርት ማስረጃዎች፣ የድጋፍ ደብዳቤዎች ወይም ሌሎች የተጠየቁ ሰነዶችን ማስታወቂያው ባዘዘው መልኩ ያያይዙ። ለምሳሌ፣ ማመልከቻው ሲቪ እና የመሸፈኛ ደብዳቤ ብቻ እንዲቀርብ ሲጠይቅ፣ ተጨማሪ የትምህርት ማስረጃዎችን ወይም ሰርተፍኬቶችን ማያያዝ አያስፈልግም። ይህ አላስፈላጊ መጨናነቅን ከመፍጠር ባሻገር ማስታወቂያውን በሚገባ አለማንበብዎን ያሳያል።
● የማመልከቻ ቀነ-ገደብን ያክብሩ: የመጨረሻውን የማመልከቻ ቀን በጥንቃቄ ይመልከቱ እና ከቀነ-ገደቡ በፊት ማመልከቻዎን ያስገቡ። ዘግይተው የሚቀርቡ ማመልከቻዎች ወዲያውኑ ውድቅ ይሆናሉ።
📍ጠቃሚ ምክር: “ለአንዱ ሥራ ያመለከትንበት ማመልከቻና የትምህርትና የልምድ መዘርዝር (ሲቪ) ምንም ሳይለወጥ ለሌላ ሥራም ሊሆን ከቶ አይችልም።” ይህንን አስታውሱ! እያንዳንዱን ማመልከቻ ለሚያመለክቱበት ስራ እንዲስማማ አድርገው ያዘጋጁ።
2. ያልተጠናቀቁ ነገሮችን አለመጥቀስ
የተጠናቀቀውን ብቻ ይፃፉ:
ብዙ አመልካቾች “ማስተርስ እየተማርኩ ነው” ወይም “የመመረቂያ ፅሁፍ ይቀረኛል” የሚሉ ሀረጎችን በሲቪያቸው ላይ ይጽፋሉ። ቀጣሪው ሙሉ ጊዜውን ለስራው የሚሰጥ ሰው ነው የሚፈልገው እንጂ ገና ትምህርቱን ያልጨረሰን ሰው አይደለም። የጨረሱትን ትምህርት ወይም ኮርስ ብቻ ይጥቀሱ። ያልጨረሱት ትምህርት በአሁን ሰዓት ለስራው ትርጉም አይኖረውም።
3. የማመልከቻ ሰነዶችን ጥራት ማረጋገጥ
● ንጹህ እና ግልጽነት ያላቸው ሰነዶችን ይላኩ: የማይነበብ፣ ደብዛዛ ወይም ፎቶኮፒ የተደረገ ማመልከቻ እና ሲቪ መላክ ለስራው ያለዎትን ዝቅተኛ ተነሳሽነት ያሳያል። ሁሉም ሰነዶችን ዲጂታል ከሆነ በከፍተኛ ጥራት (High Quality) ፒዲኤፍ (PDF) አድርገው ይላኩ። የታተመ ከሆነም ንጹህ እና የሚነበብ መሆኑን ያረጋግጡ። ስህተት ያለበትን የሲቪ ፎቶ ኮፒ ደግሞ በጭራሽ አይላኩ!
የማህበራዊ ሚዲያ ተሳትፎዎን ይገምግሙ: አንዳንድ ቀጣሪዎች የአመልካቾችን የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች ይፈትሻሉ። በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚለጥፏቸው ነገሮች ስብዕናዎን፣ የስራ ሞራልዎን እና ሙያዊ አቋምዎን ሊያንጸባርቁ ስለሚችሉ ጥንቃቄ ያድርጉ።
4. የሲቪ እና የማመልከቻ ደብዳቤ ዝግጅትን ማሻሻል
● ከሌሎች ግብዓት ያግኙ: የማመልከቻ ደብዳቤ እና ሲቪ ከመላክዎ በፊት ለሌላ ሰው አሳዩ። የሌላ ሰው አይን የእርስዎን ስህተቶች ለማየት ይረዳል። እንዲሁም በኢንተርኔት ላይ የሚገኙ ነፃ ናሙናዎችን (templates) በመጠቀም በዚያ እየተመሩ መጻፍ ይችላሉ። “ድፍረት እውቀት አይሆንምና ዝም ብሎ መድፈር የትም አያደርስም።” ከእኛ የተሻሉ ሰዎችን ማማከር ሁሌም ይጠቅማል።
የፊደል እና የሰዋስው ስህተቶችን ያስወግዱ: ማመልከቻዎ ላይ የፊደል ግድፈቶች (typos) ወይም ሰዋሰዋዊ ስህተቶች አለመኖራቸውን ያረጋግጡ። ኮምፒውተር ላይ ያሉ የ”Spell check” መሳሪያዎችን መጠቀም ይችላሉ። አንድ ስህተት እንኳ የሌለበት ማመልከቻ ለመላክ ይጣጣሩ።
● ሙያዊ ቅርፅ ይኑር: ማመልከቻዎን በተለያዩ ቀለማት አይዥጎርጉሩ። ደመቅ እና ፈዘዝ ያሉ ፊደላትን ያለ አግባብ አይጠቀሙ። እነዚህ ነገሮች ሙያዊነት የሌላቸው ከመሆናቸውም በላይ ለማየትም ደስ አይሉም።
5. ትርጉም የሌላቸውን ነገሮች ከመጥቀስ መቆጠብ
● የተመረቁበትን ነጥብ (CGPA) በጥንቃቄ ይጥቀሱ: በቀጥታ ካልተጠየቁ ወይም ነጥብዎ ለስራው ትልቅ ጥቅም የሚያስገኝ ካልሆነ በስተቀር የተመረቁበትን ነጥብ (CGPA) ጠቅሰው መፃፍ አያስፈልግም። ቀጣሪው ስለ ማንነትዎ የማመልከቻዎን አፃፃፍ በማየት ብቻ ግምት ሊወስድ እንደሚችል ያስታውሱ።
● 6. ተገቢ የመገናኛ ዘዴዎችን መጠቀም
የተጠቀሰውን ህግ ያክብሩ: የስራ ማስታወቂያው ለመገናኛ ያስቀመጠውን ህግ ያክብሩ። “በስልክ አይጠየቅ” ከተባለ መደወል የለብዎትም። ማስታወቂያው በኦንላይን ፖርታል ብቻ እንዲቀርብ ሲጠይቅ ኢሜይል መላክ ተገቢ አይደለም።
እነዚህን ነጥቦች በመተግበር፣ የስራ ማመልከቻዎ ሙያዊ እና ተፈላጊ ሆኖ እንዲቀርብ ማድረግ ይችላሉ። መልካም የስራ ፍለጋ!